1 Chronicles 5

ሮቤል

1የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሮቤል የበኵር ልጅ ቢሆንም፣ የአባቱን መኝታ ስላረከሰ፣ የብኵርና መብቱ ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጥቷል። ከዚህም የተነሣ ትውልዱ የበኵርነቱን ተራ ይዞ ሊቈጠር አልቻለም። 2ይሁዳ ከወንድሞቹ ይልቅ ብርቱ ነበረ፤ ገዥ የወጣው ከእርሱ ቢሆንም፣ የብኵርና መብቱ የተላለፈው ለዮሴፍ ነበረ። 3የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ወንዶች ልጆች፤

ሄኖኅ፣ ፋሉሶ፣ አስሮን፣ ከርሚ።
4የኢዩኤል ዘሮች፤
ልጁ ሸማያ፣ ልጁ ጎግ፣
ልጁ ሰሜኢ፣
5ልጁ ሚካ፣
ልጁ ራያ፣ ልጁ ቢኤል፣
6የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ማርኮ የወሰደው ልጁ ብኤራ።
7የቤተ ሰቡ የዘር ትውልድ በየጐሣ በየጐሣው ሲቈጠር እንደሚከተለው ነው፤
የጐሣ አለቃ የሆነው ኢዮኤል፣ ዘካርያስ፣
8የኢዮኤል ልጅ፣ የሽማዕ ልጅ፣ የዖዛዝ ልጅ ቤላ፣ እነዚህ ከአሮዔር እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በሚገኘው ምድር ላይ ሰፈሩ። 9ከብቶቻቸው በገለዓድ ምድር በዝተው ስለ ነበር፣ በምሥራቅ በኩል ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ምድረ በዳው ዳርቻ ድረስ የሚገኘውን ምድር ያዙ።

10በሳኦልም ዘመነ መንግሥት በእጃቸው ተመትተው ድል ከተደረጉት አጋራውያን ጋር ተዋጉ፤ በመላው የገለዓድ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙትን መኖሪያዎቻቸውን ያዙ።

ጋድ

11የጋድ ነገድ ደግሞ ከእነርሱ ቀጥሎ እስከ ሰልካ ድረስ በሚገኘው በባሳን ምድር ኖሩ፤

12አለቃው ኢዮኤል፣ ሁለተኛው ሳፋም ከዚያም ያናይና ሰፋጥ ሆነው በባሳን ተቀመጡ።
13ቤተ ዘመዶቻቸውም በየቤተ ሰቡ እነዚህ ነበሩ፤
ሚካኤል፣ ሜሱላም፣ ሳባ፣ ዮራይ፣ ያካን፣ ዙኤ፣ ኦቤድ፤ በአጠቃላይ ሰባት ነበሩ።
14እነዚህ ደግሞ የቡዝ ልጅ፣ የዬዳይ ልጅ፣ የኢዬሳይ ልጅ፣ የሚካኤል ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የኢዳይ ልጅ፣ የዑሪ ልጅ፣ የሑሪ ልጅ፣ የአቢካኢል ልጆች ናቸው።
15የቤተ ሰባቸውም አለቃ የጉኒ ልጅ፣ የአብዲኤል ልጅ አሒ ነበረ።

16ጋዳውያንም በገለዓድ፣ በባሳንና እስከ ዳርቻዋ በሚገኙት መንደሮች እንዲሁም በሳሮን በሚገኙ የግጦሽ ስፍራዎች ሁሉና ከዚያም ወዲያ ዐልፈው ተቀመጡ።

17እነዚህ ሁሉ በትውልድ መዝገብ የሰፈሩት በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታምና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነው።

18የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ አርባ አራት ሺሕ ሰባት መቶ ስድሳ ብቁ የጦር ሰዎች ነበሯቸው። እነርሱም ጋሻ መያዝ፣ ሰይፍ መምዘዝና ቀስት መሳብ የሚችሉ ጠንካራና በውጊያ የሠለጠኑ ናቸው። 19እነዚህም በአጋራውያን፣ በኢጡር፣ በናፌስ፣ በናዳብ ላይ ዘመቱ። 20በጦርነቱም ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው ስለ ነበር፣ በውጊያው ረዳቸው፤ አጋራውያንንና የጦር አጋሮቻቸውን ሁሉ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ስለ ታመኑበትም ጸሎታቸውን ሰማ። 21የአጋራውያንንም እንስሶች ማረኩ፤ እነዚህም አምሳ ሺሕ ግመሎች፣ ሁለት መቶ አምሳ ሺሕ በጎችና ሁለት ሺሕ አህዮች ነበሩ። እንዲሁም አንድ መቶ ሺሕ ሰው ማረኩ። 22ውጊያው የእግዚአብሔር ስለ ነበር፣ ሌሎችም ብዙ ሰዎች ተገደሉ። እስከ ምርኮ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ በእጃቸው ነበረች።

እኩሌታው የምናሴ ነገድ

23የምናሴ ነገድ እኩሌታ ሕዝብ ቍጥር ብዙ ነበረ፤ እነርሱም ከባሳን ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔም ድረስ ባለው ምድር ሰፈሩ፤ ይህም እስከ ሳኔር አርሞንዔም ተራራ ድረስ ማለት ነው።

24የየቤተ ሰቡም አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፤ ይሽዒ፣ ኤሊኤል፣ ዓዝርኤል፣ ኤርምያ፣ ሆዳይዋ፣ ኢየድኤል፤ እነዚህ ጀግና ተዋጊዎች፣ የታወቁ ሰዎችና የየቤተ ሰባቸው አለቆች ነበሩ። 25ይሁን እንጂ ለአባቶቻቸው አምላክ ታማኞች አልሆኑም፤ እግዚአብሔር ከፊታቸው ያጠፋቸውን የምድሪቱን አሕዛብ አማልክት በማምለክ አመነዘሩ። 26ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ ይኸውም የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አነሣሥቶ የሮቤልን፣ የጋድንና፣ የምናሴን ነገድ እኩሌታ ማርኮ እንዲወስድ አደረገ። እነዚህንም ወደ አላሔ፣ ወደ አቦር፣ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ ዳርቻ አፈለሳቸው፤ እነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።

Copyright information for AmhNASV